"የፀረ-ሙስና ትግሉ የህዝብና የመንግሥት ቋሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት'' ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ሎሚ በዶ
"የፀረ-ሙስና ትግሉ የህዝብና የመንግሥት ቋሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት''
ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ሎሚ በዶ
የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሃ-ግብር በድምቀት አክብሯል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ሎሚ በዶ ዛሬ የምናከብረው የፀረ-ሙስና ትግል ያለፈውን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን፣ ያለንበትን ለመገምገምና ወደፊት የምንመራበትን አቅጣጫ ለመወሰን የሚያስችለን ነው ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዋና መወያያ ነጥቦች መካከል ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠ አጀንዳ መሆኑን አንስተው፤ የፀረ-ሙስና ትግሉ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ የጋራ ሀገራዊ ህልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት 25 ዓመታት ኮሚሽኑ በሶስት ዋና ዋና የትግል አዕማድ ላይ ተመስርቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ የዜጎችን አስተሳሰብ የሚቀርፅ የሥነምግባር ግንባታ፣ የሌብነት ቀዳዳዎችን የሚደፍን የሙስና ቅድመ-መከላከል እና ጥፋተኞችን ለፍትህ የሚያቀርብ የህግ ማስከበር ስራዎች ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ሶስት መሰረቶች የፀረ-ሙስና ትግሉ የማዕዘን ድንጋዮች ሆነው አሁንም ያገለግላሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በ25 ዓመታት የሥራ ጉዞው በሥነ-ምግባር ግንባታ፣ በሙስና መከላከል፣ የሕዝብ ግንዛቤን በማሳደግ፣ በተቋማት የፀረ-ሙስና አቅም ማጠናከርና በተጠያቂነት ስርዓት ዝርጋታ ከሁሉ በላይ ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንፃር በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ሙስናን ለመታገል ዘመናዊ እና መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎችን በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በተለይም ሀገራዊ የጥቆማ መቀበያ ስርዓት፣ የዜጎችን ድምፅ ያለስጋት እንዲሰማ አድርጓል ብለዋል።
ሙስና የገንዘብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሥነ-ምግባር፣ የሞራል፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የልማት፣ የሀገር እና የትውልድ ግንባታ ጉዳይ በመሆኑ ሁሌም ቋሚ የህዝብና የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም ወይዘሮ ሎሚ አስገንዝበዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments