



ሀገር በትውልድ ይገነባል፤ ትውልድ ደግሞ በትምህርት ቤት ይገነባል።
የአዲስ አበባ ከተማ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በግብረ ገብና ፀረ-ሙስና ክበባት መካከል የልምድ ልውውጥ መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጀማል ረዲ እንደገለፁት በትውልድ የስነ ምግባር ግንባታ የግብረ-ገብና ፀረ-ሙስና ክበባት ሚናቸው የላቀ መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም ሀገር በትውልድ ይገነባል ትውልድ ደግሞ በትምህርት ቤት ይገነባል ያሉ ሲሆን ኮሚሽኑ "ስነ ምግባር ያሸልማል" በሚል ከትምህርት ውጤታቸው ጎን ለጎን በስነ ምግባር የተመሰከረላቸው ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት መስጠቱን ጠቁመዋል።
በልምድ ልውውጥ መድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እንደገለፁት በስነ ምግባሩ የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ተቋማትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል። ትውልዱ ያወቀና የነቃ ብቻ ሳይሆን በስነ ምግባሩ የታነፀ እንዲሆን ክበቡ ከፍተኛ ሚና አንዳለው ገልፀው በዚህ ረገድ የከተማው የስነ ምግባር ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጠንካራ ስራ እየሰራ በመሆኑ በትምህርት ማህበረሰብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መቅደስ ተስፋዬ በበኩላቸው የትውልድ ስነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ስራ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ይገኛል ብለዋል። በተለይ ከትምህርት ተቋማት ጋር በርካታ ተግባራትን በማከናወን በትምህርት ቤቶች 1046 ክበባትን ተቋቋሙው ወደ ተግባር መግባታቸውን የገለፁት ም/ኮሚሽነሯ ክበባት ከመቋቋማቸው ባለፈ ያከናወኗቸውን ተግባራት በመገምገም የተሻለ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ለሌሎች በማካፈል ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመድረኩ ላይ የአራት የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ክበባት ልምድ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በከተማዋ ስር ያሉ የሁሉም ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህሮችና የግብረ-ገብና ፀረ-ሙስና ክበባት ተጠሪ መምህራኖች ታሳታፊ ሆነዋል።
"ሙስና ስጋት የማይሆንባት አዲስ አበባን እንፈጥራለን!”
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments