



ወጣቶች ህልማቸውን እንዳይኖሩ የሚያደርገውን ሙስና ለመግታት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል :–ኮሚሽነር ጀማል ረዲ
የአዲስ አበባ ከተማ የስነ-ምግባር ና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በአለም ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ የብዙሃን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በወዳጅነት ፖርክ አካሄደ።
"ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል" በሚል መሪ ቃል ነው የአካል ብቃት እንቅስቃሴው የተካሄደው።
የአዲስ አበባ ከተማ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ የአካል ብቃት እንቅስቃሴውን በአስጀመሩበት ወቅት ጤናማ፣ ብርቱ፣ ንቁ፣ ጀግና ዜጋ ማፍራት ከተቻለ ሀገርን ማበልጸግ ይቻላል ብለዋል።
ወጣቶች ትልቅ ህልም አላቸው ህልማቸውን እንዳይኖሩ እንቅፋት ከሚሆንባቸው ጉዳዮች አንዱ ሙስና ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ሙስናን ለመግታትም ሆነ በሀገር ግንባታ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ በመግታቱ ረገድ የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውሰው ወጣቶች በከተማቸው ብሎም በሀገራቸው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወጣቶች የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆኑ በፀረ ሙስና ትግሉ የበኩላቸው አስተዋፅኦ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ወጣቶች የእርስ በእርስ ትስስራቸውን በማጠናከር በአቋራጭ ከመክበር ይልቅ ሰርቶ የመለወጥ ባህልን ሊያዳብሩ ይገባል ሲሉም አቶ በላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ምክትል ኮሚሽነር መቅደስ ተስፋዬ በበኩላቸው ወጣቶች የነገ ህልማቸው መልካም እና የተሳካ እንዲሆን የፈጠረውን የሙስና ትግል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራቸውን ከሙስና የመጠበቅና በሚያገኙት አጋጣሚ ግንዛቤ በመፍጠር ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለው በመድረኩ የተገኙ እና ያስተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል
ዛሬ በወዳጅነት ፓርክ በድምቀት በተካሄደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም ላይ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ10ሺህ በላይ ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና የስፓርት ቤተሰቦች ተሳትፈውበታል።
“ሙስና ስጋት የማይሆንባት አዲስ አበባን እንፈጥራለን!”
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments